Wednesday, December 4, 2013

ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወዳገራቸው የመመለስ ግዴታው የህወሃት/ኢህአዴግ ነው!

ኦባንግ ለቴድሮስ መልክት ላኩ

obang and tedros


ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)
ኅዳር 23፣ 2006 ዓም
ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወዳገራቸው የመመለስ ግዴታው የህወሃት/ኢህአዴግ ነው!
ግልጽ ደብዳቤ ለሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም ገ/የሱስ

____________________________________________________________
ለዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ
ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም፤
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ኢትዮጵያውያንን በቀለም፣ በዘር፣ በጎሣ፣ በቋንቋ፣ በጾታ፣ በክልል፣ ወዘተ ሳይከፋፍል በየትኛውም የዓለም ክፍል (ኢትዮጵያንም) ጨምሮ የሚደርስባቸውን ማንኛውም ዓይነት ማኅበራዊ ኢፍትሃዊነት ለመከላከል፣ ለማስቆም፣ ለማጋለጥ፣ ወዘተ እና ባሉበትም ቦታ ሁሉ ከፈጣሪ የተሰጣቸውን መብት ለማስጠበቅ የቆመ ድርጅት ነው፡፡ ሆኖም ግን እኔ ኦባንግ ሜቶ ይህንን ደብዳቤ የምጽፍልዎ የዚህ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር እንደመሆኔ ብቻ ሳይሆን የውቢቷ ኢትዮጵያ የደም ውጤት በመሆኔ እንደ አንድ ወንድም በመሆንም ጭምር ነው፡፡
ይህንን ደብዳቤ የምጽፍልዎ እርስዎንም ሆነ እርስዎ አባል የሆኑለትን የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና ኢህአዴግን ለመለመን ወይም ለማስደሰት ሳይሆን በሳዑዲ አረቢያና በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ውስጥ በኢትዮጵያዊ ሕዝቤ ላይ እየደረሰ ያለውን ከሰብዓዊነት ውጪ የሆነ አሰቃቂ ተግባር የማስቆምና አስቸኳይ መፍትሔ የማምጣት ግዴታ ህወሓት/ኢህአዴግ እንዳለበት ለማስታወቅ ነው፡፡
በመሆኑም እኔና እርስዎ የፖለቲካም ሆነ የአስተሳሰብ ልዩነት እንዳለን ግልጽ ቢሆንም አገር “እየመራሁ ነኝ” የሚለው ህወሃት/ኢህአዴግ የኃላፊነት ቦታ ላይ ያስቀመጥዎት እርስዎን በመሆኑ ይህ ጉዳይ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ሰዎች አንዱ ነዎት፡፡ ከሥልጣኑም ጋር አብሮ ከፍተኛ የሆነ ኃላፊነት ይመጣል፤ ይህም በሁሉም ዘንድ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግም የሕዝብ ውክልና ባይኖረውም እንኳን ለእያንዳንዱ ነገር በቀጥታ ተጠያቂ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ደብዳቤ ላይ የማሰፍራቸው ነጥቦች እርስዎንም ሆነ ህወሃት/ኢህአዴግን የሚያስደስት ላይሆን ይችላል፡፡ በተለይ በሳዑዲና በሌሎች የመካከለኛ ምስራቅ አገራት በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ግፍ በዓለም ዙሪያ ተበትነው በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ ያሳረፈው ተጽዕኖና ኃፍረት እንዲሁም ቁጭት ይህ ነው ተብሎ የሚነገር እንዳልሆነ ህወሃት/ኢህአዴግ በሚከተለው የመረጃ ማፈን ፖሊሲ የኢትዮጵያ ሕዝብ መመልከት ባይችልም እርስዎና አብሮዎት ያሉት ሳታዩት ያለፋችሁት ጉዳይ አይደለም፡፡ይህንን ደብዳቤ የምጽፍልዎ መረጃን በመመርኮዝ በመሆኑ ለምጽፈው እያንዳንዱ ነገር ሙሉ ኃላፊነት በመውሰድ መሆኑን አስቀድሜ ላስገነዝብዎት እወዳለሁ፡፡
ባለፉት ሳምንታት በ30 አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በ80 ከተሞች ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ በአንድ ድምጽ በሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ ይቁም በማለት ቁጣችንን ስናሰማ ቆይተናል፤ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ይህ እየተደረገ ያለበት ምክንያትም በሳዑዲ ያሉት ኢትዮጵያውያን ከአንድ የተወሰነ ክልል ወይም የአንድ ጎሣ ቋንቋ ተናጋሪ ወይም የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ወዘተ ስለሆኑ ሳይሆን በቅድሚያ ሰብዓዊ ፍጡራን ስለሆኑ ከዚያም በላይ የእኛንም ኢትዮጵያዊነት ማንነትና ክብር የሚነካ በመሆኑ ነው፡፡ታዲያ ለዚህ ቀውስ መፍትሔው ለመንገድ ሥራ እንደሚገኝ ድጎማ ከዓለም ባንክ ወይም ከተባበሩት መንግሥታት ወይም ከሌሎች ለጋስ አገራት ወይም ደግሞ እንደ “ህዳሴ ግድብ ቦንድ” ከዳያስፖራ የሚገኝ አይደለም፡፡ በተጻጻሪው ለዚህ ቀውስ ዋንኛውን ኃላፊነት የሚወስደውና በሳዑዲ የሚሰቃዩትን ኢትዮጵያውያንን የመታደግ ግዴታው የህወሃት/ኢህአዴግ ነው!
ይህ በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው ሰቆቃ የሁላችንንም ህልውና የነካ በመሆኑ “በእርግጥ ኢትዮጵያዊን አገር አላቸው ወይ?” ብለን እንድንጠይቅ ያደረገን ሆኗል፡፡ በተጻጻሪው ግን በህወሃት/ኢህአዴግ በኩል የሚታየው የውሳኔ አሰጣጥ እና እርምጃ አወሳሰድ አናሳነት እንዲሁም ዝግተኝት በአመራር ላይ ያሉትን ሁሉ ስለ ችግሩ ያላቸው የግንዛቤና የአመራር ደካማነት ያለአንዳች ጥያቄ በጉልህ ያሳየ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ፈርጀ ብዙ ለሆነው የኢትዮጵያ ችግር ዋንኛ ተጠያቂ ህወሃት/ኢህአዴግ ቢሆንም የችግሩ አፈታት ግን ለሥራ ባልደረቦች ጊታር የመጫወት ያህል ወይም በጥቂት ቃላት ትዊተር ላይ መልዕክት የመላክ ያህል የቀለለ እንዳልሆነ እሙን ሆኗል፡፡
በዚህ ደብዳቤ ላይ የማነሳቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩኝም በቅድሚያ መጠየቅ የምፈልገው ጥያቄ ቢኖር ለመሆኑ ጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ደሳለኝ የት ነው ያሉት? ህወሃት/ኢህአዴግም ሆነ አቶ ሃይለማርያም የህዝብ ውክልና ያላቸው ባይሆኑም የሥራ አስፈጻሚው ሥልጣን የተሰጠው ለእርሳቸው በመሆኑ በዚህ ቀውስ ጊዜ በውክልና ሳይሆን በግልጽ በመታየት የሥራ አስፈጻሚነት ተግባራቸውን መወጣት ይገባቸው እንደነበር የእኔ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ኢትዮጵያውያን በተለይም በሳዑዲ ያሉቱ ጥያቄ ሆኗል፡፡ ወይስ ሁኔታው ከዚህ በፊት ሲነገር የነበረውን እና ህወሃት/ኢህአዴግ እርስዎን ወደ ጠ/ሚ/ር መንበር ላይ ለማስቀመጥ ያለውን ውጥን እውን የማድረጊያ መንገድ በመሆኑ ይሆን? ይህ ከሆነስ የእነዚህ ወገኖቻችንን ስቃይ ለራሱ የፖለቲካ ዓላማ እየተጠቀመበት ያለው ማነው?
ሰሞኑን በቤተሰብ ምጣኔ ጉዳይ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር ባጠቃላይ ያተኮረው በሳዑዲ ስላሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ ላይ ማተኮሩ በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅና በዓለም ዙሪያ በመከራና በስቃይ ውስጥ ስላሉት ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ ስላለው ችግር ያለዎን የግንዛቤ ማነስን ወይም ግዴለሽነት የሚያሳይ ነው ከማለት ሌላ ምን ሊባል ይችላል? ምክንያቱም በመላው አረቢያ ምድር ኢትዮጵያውያን ምን ያህል እየተሰቃዩ እንደሆነ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች ለዓመታት ሲዘግቡት የኖረ፣ እኛም በየጊዜው የምናሳውቀውና ህወሃት/ኢህአዴግ በውል የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ቀውሱ ይፋ በሆነበት ሰሞን ስሜትዎ ምን ያህል እንደተረበሸና ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ በሚደርስባቸው ሰቆቃ እንዴት እንዳዘኑ ለሚዲያ ሲገልጹ የነበረው ከፖለቲካና ሚዲያ ፍጆታ ውጪ ልባዊ ስሜት ነው ብለን ለመቀበል ችግር ውስጥ ከትቶናል፡፡
በሳዑዲ አረቢያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰው ሰቆቃ በድንገት እንዳልሆነ ማንም መካድ የሚችለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ሳዑዲ የምትከተለው የከፋላ አሠራር መሠረት የአንድ ጉዞ ቲኬት ቆርጠው ወደዚያ የሚሄዱ ሁሉ ሳዑዲ አየር ማረፊ እንደደረሱ ፓስፖርታቸውን እና ሌሎች የመታወቂያ ሰነዶቻቸውን እንዲያስረክቡ ይደረጋል፡፡ ሆኖም ግን ከሳዑዲ ለመውጣት የሚፈልጉት እንኳን የመውጫ ቪዛ ለማግኘት በሚፈልጉበት ጊዜ ፓስፖርታቸውንም ሆነ ማንኛውንም መታወቂያቸውን መልሰው የማግኘት ዕድል የላቸውም፡፡ በዚህ ዓይነት አሠራር ውስጥ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ በድንበር የገቡትን ሳይጨምር ሌሎቹ ግን በተሠጣቸው የሰባት ወር ምህረት ጊዜ የመጓጓዣ ሰነዶቻቸው እጃቸው ላይ ሳይኖር በተፈቀደው ጊዜ ለመጠቀም የሚችሉበት ሁኔታ ሊከሰት አልቻለም፡፡ ሰነዱ በእጆቻቸው ያሉትም እንኳን ቢሆኑ ቀውሱ በተፈጠረ ጊዜ ለመውጣት እንዳይችሉ በሳዑዲ ወሮበሎችና ፖሊሶች የደረሰባቸው ሰቆቃ በሁኔታው ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ እንዳያመጣ አድርጓል፡፡ ከዚህ ሌላም ሳዑዲ አረቢያ ሰጠች በተባለው የምህረት ጊዜ የተለያዩ አገራት ዜጎቻቸውን በቻሉት ሁኔታ ሁሉ እያስወጡ ባሉበት ጊዜ ኢትዮጵያውያኑን የሚታደግ መታጣቱ መልስ የሚያሻውና በኃላፊነት የሚያስጠይቅ ነው፡፡ (ይህንን ጉዳይ ከዚህ በፊት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ባወጣው ደብዳቤ ላይ ተዘርዝሯል)
ችግሩን ወደኋላ መለስ ብለን ስንቃኘው ሰቆቃው የጀመረው ከጥቂት ሳምንታት ወይም ከጥቂት ወራት ወይም ጊዜያት በፊት ሳይሆን ለዓመታት የቆየና በተለይም ከስድስት ዓመታት ጀምሮ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ወደ አረቢያ ምድር መፍለስ በጀመሩበት ጊዜ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ዋንኛው ምክንያት ህወሃት/ኢህአዴግ የሚከተለውና ጥቂቶችን በመጥቀም ሌሎችን የሚያገልለውና አገር አልባ የሚደርገው ፖሊሲ በርካታ ዜጎችን አገራቸውን እንደ አገር እንዲቆጥሯት ስላላደረጋቸው ነው፡፡ በመሆኑም በአገሩ ሁለተኛና ከዚያ በታች ዜግነት ተሰጥቶት በተወለደባት አገር ስደተኛ የሆነ ሁሉ በሌላ አገር ሄዶ እውነተኛ ስደተኛ ለመሆን ለምን ይፈልጋል ብሎ የሚጠይቅ አእምሮ ቢስ ነው ቢባል ማስረጃ የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን እንደዚህ ዓይነት ውሳኔው ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ ሁሉ በአረብ ምድር እየደረሰ ያለውን ሰቆቃ እየሰሙ መሆኑ የሚካድ ባይሆንም የኢኮኖሚ ስደተኞች እንደመሆናቸውና ባገራቸው እንደዜጋ ተቆረው ኢኮኖሚያዊ ችግራቸውን ማቃለል አለመቻላቸው ኢሰብዓዊነት በተጠናወታቸውና ጨካኝ የአራዊት ባህርይ ባላቸው አረቦች እጅ እያወቁ እንዲወድቁ አስገድዷቸዋል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፤ በአረብ ምድር ያለው ሁኔታ ችግር አልባ የሆነ ይመስል ህወሃት/ኢህአዴግ ዝም ባለበትና በግልጽም ይሁን በእጅ አዙር ተጠቃሚ በሆነበት በዚህ የሰው ማዘዋወርና ኢትዮጵያውያንን የመሸጥ ድርጊት እንደ መልካም ንግድ በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ውስጥ (የገጠር ቦታዎችም ጭምር) ትልልቅ ማስታወቂያዎች (ቢልቦርድ) እየተሰራላቸው ንግዱ ሲጧጧፍ ቆይቷል፡፡ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚሄዱ በተለይ ሴቶች እህቶቻችን የሚደርስባቸው ሰቆቃ በሰው አእምሮ የሚታሰብ አለመሆኑ በሚነገርበትና ከበቂ በላይ ማስረጃዎች በሚቀርቡበት ጊዜያት ሁሉ ምንም ዓይነት የቀረበ መፍትሔ የለም፡፡ ለመሆኑ በቅርቡ በአረቢያ በሚገኙ የአእምሮ ተቋማት ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ በሽተኞች ኢትዮጵያውያን ሴቶች መሆናቸው ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ ምን የተወሰደ እርምጃ ይኖር? እርስዎስ የውጭ ጉዳይ መንበር ላይ እንደመቀመጥዎ ይህንን ሁሉ ሰቆቃ እየሰሙ እስካሁን ትልልቅ ማስታወቂያ የተሰራላቸውን ወደ አረቢያ ኢትዮጵያውያንን የሚያግዙትን ድርጅቶች እንዲዘጉ ያላደረጉት ለምን ይሆን? ይህንን ከማድረግ ይልቅ ራስዎ የሚመሩት መ/ቤት ድረገጽ ባለፈው ዓመት ብቻ 160ሺህ ኢትዮጵያውያን ለቤት ሠራተኛነት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለማቅናት መፈለጋቸውን መዘገቡ በምን ቋንቋ የሚገለጽ ይሆን? እነዚህ ወገኖች ለሰቆቃ፣ ለመከራ፣ አስገድዶ ለመደፈር፣ ያለዋጋ ለመሥራት እንዲሁም ለመሞት እየተጋዙ መሆናቸው እየታወቀ ዝም መባሉ ምን ዓይነት አስረጅ የሚቀርብበት ይሆን? ለመሆኑ ከዚህ የደም ገንዘብ እያተረፈ ያለው ማነው? እኔ አላውቅም የሚለው በቂ ምላሽ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም፤ እንደ ምላሽ እንቀበለውም ከተባለ እንኳን የዛሬ 30ዓመት አካባቢ እርስዎ አሁን የተቀመጡበት ወንበር ላይ የነበሩትና ደርግ የሚከተውን ፖሊሲ በመቃወም ሥልጣናቸውን የለቀቁትን የኮ/ሎ ጎሹ ወልዴን ፈለግ መከተል አንድ አማራጭ የሚጠቀስ ብቻ ሳይሆን በታሪክም የሚታወስ ተግባር ነው፡፡ ከልቡ ያዘነ ሆኖም ፓርቲው የሚከተለው ፖሊሲ ከራሱ ኅሊና ጋር የተጋጨበት የሚወስደው ውሳኔ በመሆን ለትውልድ የሚያልፍ አኩሪ ተግባር ነው፡፡
ሚ/ር ቴድሮስ፤
እርስዎ አባል የሆኑበት ህወሃት/ኢህአዴግ የደርግ አገዛዝን “ሰው በላ” እያለ ይክሰሰው እንጂ ህወሃት/ኢህአዴግ በአሁኑ ጊዜ እየፈጸመ ያለው ተግባር “ሰው በላ” ብቻ የሚያስብለው ሳይሆን “ሰው አስበዪ” የሚያስብለውም ጭምር ነው፡፡ እንደ ማስረጃም፡- እርስዎ በሳዑዲ በሚገኙ ኢትዮጵያውያ ሰቆቃ ዕንቅልፍ ነስቶኛል ባሉበት ሰሞን እንዲሁ ሰቆቃው ከዕንቅልፍ በላይ የነሳቸው ወገኖች በአዲስ አበባ በሚገኘው የሳዑዲ ኤምባሲ ፊት የተቃውሞ ሃሳባቸውን ለመናገር በተሰበሰቡበት በፌዴራል ፖሊስና በደኅንነት ኃይሎች መደብደባቸውና ሰልፉ መበተኑ የዓለም ህዝብ ተመልክቶታል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የእኔም ጥያቄ እርስዎ በሳዑዲ ለሚሰቃዩት ዕንቅልፍ እስኪያጡ ካዘኑላቸው ምነው ያው እንቅልፍ ማጣት በፌዴራል ፖሊስ ለተደበደቡት ተግባራዊ ሳይሆን ቀረ? ወይስ በሳዑዲ የደኅንነት ኃይላት የሚደርሰው ሰቆቃ በፌዴራል ፖሊስ ከሚደርሰው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ሆኖ ይሆን? ወይስ ከኢትዮጵያ ውስጥና ውጭ ያሉ የህመም አሸካከማቸው የተለያየ ይሆን?እንደ እውነቱ ከሆነ አዲስ አበባ ላይ የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት ከወጡት ጋር እርስዎም እንደ ዜጋ እና የጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤትነት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ አብረው በሰልፉ ሊገኙና ተቃውሞዎን ሊያሰሙ በተገባ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ተነሳሽነት በሌለበት እና ለወገኖቻቸው መብት የሚቆሙት ሁሉ በሚረገጡበትና አገር አልባ መሆናቸው እንዲሰማቸው በሚደረግበት ጊዜ ሳዑዲዎች ለምን ኢትዮጵያውያንን እንዲህ እንደሚሰቃዩ ለተጠየቀው አንዱ የሳዑዲ ተወላጅ “እኛን ከምትረግሙና ከምትኮንኑን በመጀመሪያ የራሳችሀ መንግሥት እንደ ሰው እንዲቆጥራችሁ አድርጉ” በማለት የመለሰው ሁኔታውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
እንደ እኔ እምነት የሰው ዘር በሙሉ ከፈጣሪ የተሰጠው በማንም የማይገሰስ መብት ስላለው ሁሉም ሰው በእኩል ዓይን ሊታይ ይገባዋል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ይህ መመሪያ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል፡፡ ከንፈር መምጠጥ ከሚመስል የታይታ ዕርዳታም ሆነ ሥራ ይልቅ እውነተኛ ሥራ በተግባር ሊታይ ይገባል፡፡ እውነተኛ “ዕድገትና እና ትራንስፎርሜሽን” የሚያስፈልገው በዚህ ሰብዓዊ በሆነ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ከዚህ የሚቀድም ነገር ሁሉ ከሰብዓዊነት ተራ የወጣ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለውና ዘላቂ ለውጥ የማያመጣ ነው፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በስቃይ ላይ በሚገኙት ኢትዮጵያውያን ስም እና ከስደተኛ ኢትዮጵያውያን ጋር ለዓመታት በመሥራት ባለኝ ኃላፊነት ሁሉን ዓቀፍና አጠቃላይ የሆነ ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ሰብዓዊ ፍጡርን የማዳኑ ሥራ ባስቸኳይ መካሄድና መጠናቀቅ እንዳለበት ላሳስብዎ እወዳለሁ፡፡ ይህንን ማድረግ ደግሞ ህወሃት/ኢህአዴግ ለኢትዮጵያውያን የሚውለው ውለታ ወይም የሚፈጽመው መልካም ነገር ሳይሆን በቅድሚያ የችግሩ ፈጣሪ በመሆኑ ኃላፊነቱ የራሱ ነው፡፡ ሲቀጥልም እንደ እርስዎ በኃላፊነት የተቀመጣችሁ ሁሉ ይህንን ማስፈጸም በቦታው ላይ ስትቀመጡ የገባችሁበት ግዴታና በኃላፊነት የምትጠየቁበትም ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡
ይህ ቀውስ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በሳዑዲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያሳየው ግዴለሽነትና ተግባርን በሥርዓት ያለመወጣት ችግር በደረሰው ችግር ላይ ተጨማሪ ሰቆቃ በመፍጠር በወገኖቻችንን ስቃይ ላይ አስከፊ ጠባሳ ጥሏል፡፡ ከዚያም አልፎ በእንዲህ ዓይት የቀውስ ወቅት ያለውን ኃይል ሁሉ በማስተባበር 24ሰዓት ሊሰራ የሚገባው ኤምባሲ አንዴ ሥራውን ሲያቋርጥ አልፎም ለሦስት ቀናት በሩን በመዝጋት “አገልግሎት አንሠጥም” በማለት ማስታወቂያ መለጠፉ በኤምባሲው ውስጥ ያሉትን ኃላፊዎች አምባሳደሩንም ጨምሮ በሥነምግባርና በሕግ የሚያስጠይቅ ነው፡፡ ይህ ክስተት የኤምባሲው ከፍተኛ ኃላፊዎችና አምባሳደሩ ሠራተኞችን ወደ ሳዑዲ በማስመጣት ህገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው የትርፉ ተጠቃሚዎች ናቸው እየተባለ ለጋራ ንቅናቄያችን ሲደርስ የነበረውን መረጃ እውነትነት ወደ ማመኑ እንድንደርስ ያደረገን ነው፡፡ እርስዎም የአምባሳደሮች አለቃ እንደመሆንዎ ባለው አጠቃላይ ሁኔታ ላይ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ሲገባዎ ዝምታን መምረጥዎ የጥፋቱ ተባባሪ ያደርግዎታል፡፡
ሌላው በዚህ ደብዳቤ ላይ ላነሳው የምፈልገው ጉዳይ ከሳዑዲ አረቢያ የሚመለሱትን ወገኖቻችን በተመለከተ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በትዊተር ላይ የሚልኩት መልዕክት ብዙዎቻችንን ግራ ያጋባ ስለመሆኑ ነው፡፡ እስከ ህዳር 19፤ 2006 ቀን ድረስ 55392 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢ መመለሳቸውን ጽፈዋል፡፡ በአማካይ ኤርባስ ወይም ቦይንግ አውሮፕላን በአንድ በረራ 400 ሰው ይጭናሉ፤ እርስዎ ተመለሱ ያሉትን ያህል ሰዎች ለማመላለስ ወደ 140 ከሳዑዲ አዲስ አበባ በረራ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ይህንን ያህል በረራ ለመካሄዱ ግን የሰጡት ምንም ዓይነት ፍንጭ ሆነ መረጃ የለም፡፡ በቀን ስንት በረራ እንደሚደረግ፣ በእያንዳንዱ በረራ ውስጥ ምን ያህል ወገኖቻችን እንደሚሳፈሩ፣ ተመላሾች ቦሌ ከደረሱ በኋላ ወደ የት እንደሚገኙ፣ ወዘተ ዝርዝር መረጃ ከእርስዎም ሆነ ከሌሎች ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ማግኘት አልተቻለም፡፡ የጋራ ንቅናቄያችን ባሉት መረጃ አቀባዮችና እኔም በቀጥታ ጉዳዩን ስንከታተል የተረዳነው ነገር ቢኖር እስካሁን እጅግ ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ የማጎሪያ ጣቢያዎች ውስጥ ያለ በቂ ምግብ፣ ውሃና መሠረታዊ ፍላጎት ማሟያዎች እየተሰቃዩ እንዳሉ ነው፡፡ ቦሌ ደርሰዋል የተባሉትም ይህንን ያህል ቁጥር ያላቸው ሳይሆኑ በጥቂት መቶዎች የሚቆጠሩ መሆናቸውን ነው፡፡ ይህ የእርስዎ የትዊተር መረጃ ትንታኔ ሊሰጥበት የሚያሻው ነው፡፡ ይህንንም የመስጠቱ ኃላፊነት የማንም ሳይሆን የመረጃ አቀባዩ የራስዎ ነው፡፡ አለበለዚያ ህወሃት/ኢህአዴግ ቁጥር ነክ በሆኑ ጉዳዮች የሚያደርገውንና የኢትዮጵያን “የኢኮኖሚ ዕድገት ድርብ አኻዝ ነው” በማለት ለዓመታት ሲፈጽም እንደነበረው የቁጥር ጨዋታ ተዓማኒነት የሌለው አድርገን የምንወስደው ይሆናል፡፡
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ለዓመታት በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ እኔም የጋራ ንቅናቄው ዋና ዳይሬክተር በመሆን እነዚህን ወገኖች እንደ መንግሥት የሚታደጋቸው ባጡበት ሁኔታ እጅግ በርካታ የሆኑ ወገኖቼን ስቃይ በቅርብ የመመልከትና የመካፈል አጋጣሚዎች ላይ ተገኝቻለሁ፡፡ በእስር ቤት ሲንገላቱ የነበሩትን፣ ሰብዓዊ ፍጡር ሊያልፍበት በማይችልበት ስቃይ ውስጥ የነበሩትን በዓለም ዙሪያ እየሄድኩ የማነጋገር እና ከእስር የማስፈታት ተግባራትን በመፈጸም ካካበኩት ልምድ አንጻር አሁን በሳዑዲ አረቢያ በተከሰተው ቀውስና በአጠቃላይ በመካከለኛው ምስራቅ ስለሚገኙት ወገኖቻችን ጉዳይ የሚከተሉት የመፍትሔ ሃሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
የመፍትሔ ሃሳቦች፡-
  1. ህወሃት/ኢህአዴግ ህዝብና ሚዲያ ሊመሰክር በሚችልበት መልክ የመጓጓዣ አውሮፕላኖችንና መርከቦችን በማዘጋጀት በስቃይ ላይ ያሉትን ወገኖቻችንን በአስቸኳይ በብዛትና በፍጥነት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይገባዋል፡፡ ይህንን ለማከናወን የኢትዮጵያ አየር መንገድንም የመደጎም፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጓዦችን የሚጭኑ መርከቦችን የማዘጋጀት ኃላፊነት አለበት፡፡ መርከቦች ጅቡቲ ዜጎቻችንን ጭነው ወደብ በሚደርሱበት ጊዜ ባስቸኳይ በርካታ የመጓጓዣ አውቶቡሶችን በማዘጋጀት ወደ አዲስ አበባና ሌሎች ዋና ዋና ከተሞች እንዲደርሱ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህንን ወጪ የመሸፈን ኃላፊነት ከአገዛዙ ጀምሮ እስከ ኤፈርትና ሌሎች የህወሃት/ኢህአዴግ የንግድ ሸሪኮች እንዲፈጽሙ ማድረግ በአደጋ እና ቀውስ ወቅት የሚጠበቅ ከመሆን ባሻገር አንድ ኃላፊ ለተሰጠው ቦታ መመጠኑን የማሳያና ብቃቱም መለኪያም ነው፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ መሠረት ግን ስደተኞቹን በማጓጓዝ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ እየወሰደ ያለው የሳዑዲ መንግሥት ስለሆነ ህወሃት/ኢህአዴግ ግን በ“ይህንን አደረኩኝ” ስም የወገኖቻችንን ስቃይ ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሙ መቆም አለበት፡፡
  2. የሳዑዲ አረቢያ በአሁኑ ጊዜ በተግባር ላይ ያዋለችውን የከፋላ አሠራር በተመለከተ ግልጽ ውይይት በማድረግ ወደ ስምምነት ውሳኔ መደረስ አለበት፡፡ በአሠራሩ ውስጥ ያለውን የተበላሸና ለሙስና የተጋለጠውን አካሄድ እንዲሁም ወደ ሳዑዲ የሚመጡ ሁሉ ለችግር እንዲያጋልጣቸው የሚያደርገውን አሠራር በውይይትና በስምምነት አንድ ደረጃ ላይ እንዲደርስ በማድረግ በስቃይ ላይ የሚገኙት ወገኖቻችን በፍጥነት ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ መፈጸም አለበት፡፡ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ባልሆነ ጥፋት ፓስፖርታቸውና ሌሎች መታወቂያ ወረቀቶቻቸው ከእነርሱ ጋር ባለመሆኑ ለዚህ ዓይነት ስቃይና መከራ መጋለጣቸው በችግራቸው ላይ ተጨማሪ ችግር መፍጠሩ እየታየ እስካሁን ዝም መባሉ ተገቢ ስላልሆነ ይህ አሰቃቂ ሁኔታ ወደ መጨረሻ ውሳኔ መምጣት ይገባዋል፡፡
  3. ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የገንዘብ ወጪ ጉዳይ አንዱ አሳሳቢ እንደሆነ ይሰማ፡፡ በሳዑዲም ይሁን በሌሎች አገራት ያሉትን ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራችን ለመመለስ ህወሃት/ኢህአዴግ የኤፈርትን በተለይ ደግሞ የሳዑዲውን ባለሃብትና የኢህአዴግ “ወዳጅ” አላሙዲን ሳይጠይቅ መቅረቱ እርሳቸውም እስካሁን በጉዳዩ ላይ እንደማያገባው ሰው ዝምታን መምረጣቸው የሚያስጠይቅ ነው፡፡ የአባታቸው አገር ተወላጆች በእናታቸው አገር ወገኖች ላይ ይህንን ዓይነት ሰቆቃ ሲያደርሱ በማየት ሼክ መሐመድ አላሙዲ ራሳቸውን የኦፐሬሽኑ አካል በማድረግ የዜግነት ድርሻቸውን እንዲወጡ መጠየቅ የህወሃት/ኢህአዴግ ኃላፊነት ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ እኚህ ሰው በኢትዮጵያን አንጡራ ሃብት አሁን ለደረሱበት ብልጽግና እንዳበቃቸው የሚታወቅ ነው፤ ወደፊት በኢትዮጵያ ያላቸውን የንግድ ኢንቨስትመንት እንዲቀጥል ከፈለጉ በጉዳዩ ላይ የባለአእምሮ ውሳኔ መስጠት የሚጠቅመው ራሳቸውን ነው፡፡የዛሬውን አያድርገውና በአሁኑ ወቅት በሳዑዲ ወሮበሎች ስቃይና መከራ ከደረሰባቸው ሴቶች አንዷ እናታቸው ወይም እህታቸው ልትሆን ትችል ነበር፡፡
  4. ህወሃት/ኢህአዴግ በተደጋጋሚ “ባስቆጠረው” ያለመታመን ሬኮርድ ምክንያት አሁን እያደረኩ ነኝ የሚለው ነገር ሁሉ ተዓማኒነት የሌለው ሆኗል፡፡ እርስዎም መግለጫ ሲሰጡ መንግሥት 24 ሰዓት እየሠራ እንደሆነ ገልጸው ነበር፤ በትዊተርም ላይ የሚያቀርቡት ቁጥር ለመታመኑ ራሱን የቻለ አጠያያቂ ጉዳይ ነው፡፡ ስለሆነም አሠራሩ በሙሉ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ፍትሐዊ አሠራር እየተካሄደ መሆኑን ለማሳመን እንዲቻል ስደተኛ ወገኖቻችንን ወደአገራቸው የመመለሱን አጠቃላይ ሂደት ዓለምአቀፉን የስደተኛ ድርጅት (IOM) ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና ሌሎች ተዓማኒነት ያላቸው ድርጅቶች በሚሳተፉበትና በሚታዘቡበት መልኩ ግልጽ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አሠራሩ ግልጽ ሆኖ ሕዝብ ይታዘብ፣ መልስም ይስጥበት፡፡
  5. በአሁኑ ጊዜ ሰቆቃው በሳዑዲ ያለ ቢመስልም በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገራትም ያሉት ወገኖቻችን በከፍተኛ ስቃይ ላይ ስለሚገኙበተለይ በየመን፣ በእስራኤል፣ በሊባኖስ፣ በዱባይ፣ በሊቢያ፣ በአረብ ኤሜሬት፣ ወዘተ እነዚህ ሁሉ ወደ አገራቸው የመመለሱ ግዴታ የህወሃት/ኢህአዴግ በመሆኑ በተለይ የከፋላ ስርዓት ተግባራዊ በሆነባቸው አገራት ለሚገኙት ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡
  6. በተደጋጋሚ በህገወጥ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ሥራ እናስቀጥራለን በማለት በሰው ማዘዋወር ንግድ ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦችና የህወሃት/ኢህአዴግ ሸሪክ ድርጅቶች መኖራቸው ሲሰማ የቆየ ነው፡፡ በተለይ በሳዑዲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በዚህ ንግድ ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለውና ወገኖቻችንን ለባርነት አሳልፎ በመስጠት ሥራ ላይ መጠመዱ ሲነገር የቆየ ነው፡፡ ይህንን የተቀናጀ የወንጀል ተግባር የእርስዎ መ/ቤትም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ነገሩ እንዳልተፈጠረ አድርገው ሲቆጥሩና ሲያድፈነፍኑት ቆይተዋል፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ ከፍተኛ ምርመራ የሚያስፈልገውና ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረብ የሚገባቸው ጊዜ ላይ በመሆኑ ከአገር ውስጥ ጀምሮ እስከ ውጭ አገር ኤምባሲዎች ድረስ በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ምርመራ መካሄድ አለበት፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀር በቀጥታ ተጠያቂው እርስዎና በተዋረድ ያሉ ኃላፊዎች መሆናቸውን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡
  7. በአገር ውስጥ በተለያዩ ከተሞች በየመንገዱ ላይ ወደ አረቢያ ምድር ሥራ እናስቀጥራለን በማለት የተለጠፉት ማስታወቂያዎች በሙሉ ባስቸኳይ መነሳት አለባቸው፡፡ በዚህ “ሥራ” ላይ የተሰማሩት በሙሉ ምርመራ እየተካሄደ ጉዳዩ ይፋ መሆን አለበት፡፡
  8. ሳዑዲዎች በወገናችን ላይ የሚያደርሱት ግፍ እየታየ አጸፋዊ እርምጃ የመውሰድ አካሄድ አለመተግበሩ አሳሳቢ ነው፡፡ የሰው መብት እየተገፈፈና እየተዋረደ፤ ወገኖቻችን እየተገደሉ ሳዑዲዎች ንግዳቸውን በአገራችን ላይ እያካሄዱ ትርፍ ሲያጋብሱ ዝም መባሉ የህወሃት/ኢህአዴግን ለወገናችን ያለውን ግዴለሽነት የሚያሳይ ከመሆን አልፎ ከዜጎቹ ይልቅ የራሱን ጥቅም የሚሳድድ ለመሆኑ በተደጋጋሚ ያሳየበት ማስረጃ ነው፡፡ ስለሆነም ጉዳዩ ወደከፋ ደረጃ በመሄድ ዜጎች የራሳቸውን እርምጃ መውሰድ ከመጀመራቸው በፊት በሳዑዲ አረቢ በነበሩት በወገኖቻችን ላይ ለደረሰው ተመጣጣኝ ባይሆንም እስካሁን የሳዑዲ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ መቆየታቸው በድጋሚ ሊጠናና ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ንብረታቸውን እያጡ እንደተባረሩ ተመሳሳይ አጸፋዊ እርምጃ በሳዑዲ ድርጅቶች ላይ ባስቸኳይ ሊወሰድ ይገባል፡፡
ለሳዑዲ አረቢያ መንግሥት፣ ሕዝብ እና አጎራባቾች በሙሉ፡
በየአገሮቻችሁ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ሠራተኞችን ላይ የምታደርሱትን ስቃይና መከራ ልታቆሙ ይገባል፡፡ ሕዝባችሁንም በዚህ ዓይነቱ ሕገወጥ ተግባር ከመሰማራት እንዲታቀብ ማስጠንቀቂያ ልትሰጡ ይገባል፡፡ በተለይ የጋራ ንቅናቄያችን ለሳዑዲ አረቢ መንግሥት የሚያስተላልፈው መልዕክት ቢኖር በአሁኑ ወቅት በአገራችሁ ላይ እየተካሄደ የሚገኘው የሰብዓዊ መብት ገፈፋ እስልምና ከሚያስተምረውም ሆነ ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) ከሰጡት መመሪያ ውጪ የሆነና ለእርሳቸው ተከታዮች በአንድ ወቅት ከለላ በመሆን ላስተናገዷቸው የሰጡትን መልካም ተግባርና ውለታ መዘንጋት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህ ዓይነት ምላሽ አይገባቸውም፤ እምነቱም አይፈቅድም፤ ባስቸኳይ ሊቆም ይገባዋል፡፡
ለሳዑዲ አረቢያውያን፡
በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ የሆነው ህግ ያስከተለውም ሆነ ወሮበሎች በዜጎቻችን ላይ የፈጸሙት የወንጀል ተግባር የአብዛኛውን ሳዑዲዎች የሚወክልና ሁሉንም በአንድ ሳጥን ውስጥ የሚያስገባቸው እንዳልሆነ የጋራ ንቅናቄያችን ያምናል፡፡ በተፈጸመው ተግባር ያዘኑና ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ የሚያደርጉ ሳዑዲዎች እንዳሉ እገነዘባለን፡፡ በዚህ መልካም ሥራችሁ እንድትቀጥሉ እናሳስባለን፤ እኛም ባለን መልካም ግንኙነት የምንቀጥልና ይህ የደረሰው ሰቆቃ ወደበለጠ የተቀራረበ ግንኙነት ሊያደርሰን የሚችል እንዲሆን እንጥራለን፡፡
ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም፡
በአገራችን ላይ ከሚደርሰው ስፍር ቁጥር ከሌለው ወንጀልና ሰቆቃ በተጨማሪ አሁን በአረቢያ ምድር እየደረሰ ያለው ችግር የጋራ ንቅናቄያችንንም ሆነ እኔን በቀጥታ በጉዳዩ ላይ እንድንቀሳቀስ አድርጎናል፡፡ ይህ የሆነው ግን እርስዎን በዚህ ሥልጣን መንበር ላይ ያስቀመጥዎና አባል የሆኑለት ህወሃት/ኢህአዴግ ለኢትዮጵያውያን ፈጽሞ ግድ የሌለውና በዘር ፖለቲካ ላይ ተጠምዶ ሁሉንም በዘር መነጽር የሚመለከት በመሆኑ ነው፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ ከመክሰር አልፎ ከጥቅም ውጭ በሆነበት ባሁኑ ወቅት እርስዎ የሚመሩት የሚ/ር መ/ቤትም ሌላ ኪሣራ ታይቶበታል፡፡ ከአገራችን ሕዝብ በታች የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች አፍሪካውያን ይህንን ዓይነት ሰቆቃ በየትኛውም አገር ሲደርስባቸው አንሰማም፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ ይህ ልባችንን የሚያደማና “ለመሆኑ ኢትዮጵያውያን አገር አላቸው?” ብለን እንድንጠይቅ ያስገደደን ነው፡፡
ፈጣሪ አሁንም ለአገራችን የምንሠራበት ሌላ ጊዜ እና አጋጣሚ እየሰጠን ያለው፡፡ ለሌሎች ልባችንን እንድናዘጋጅና በአገራችን ላይ ፍትህ፣ ይቅርታ እና ዕርቅ የሚሰፍንበትን ሁኔታዎች በሙሉ እንድናመቻችና ለተግባራዊነቱ ተግተን ልንሠራ የሚገባን ጊዜ አሁን ነው፡፡በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዜጎች በዘራቸው ወይም በቀለማቸው ወይም በቋንቋቸው፣ ወዘተ ልዩነት ሳይደረግባቸው በቅድሚያ ሰው ሆነው በመፈጠራቸው፤ ከዚያም ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው በአንድነትና በመተሳሰብ የሚኖሩባት እንድትሆን የጋራ ንቅናቄያችን ይተጋል፡፡ ፈጣሪም ይርዳን!
በዚህ ደብዳቤ ላይ ያነሳኋቸውን ነጥቦች በጥንቃቄ ተመልክተው ምላሽ መስጠት እንደሚገባዎት ላሳስብዎት ባልተገባኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ የሕዝብ ጉዳይ ስለሆነ ምላሽ መስጠቱም ለሕዝብ ጉዳይ የሚሰጡትን ትኩረት በገሃድ ስለሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ስላልሆነ ማሳሰብ እንዳለብኝ አምኛለሁ፡፡ ስለዚህ መልስዎን እጠብቃለሁ፡፡
በሳዑዲ አረቢና በመላው ዓለም በስደት በሚሰቃዩት ኢትዮጵያውያን ስም፤
ኦባንግ ሜቶ
ዋና ዳይሬክተር
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
አድራሻ፤
910- 17th St. NW, Suite 419
Washington, DC 20006 USA
ማሳሰቢያ፤ አቶ ኦባንግ ሜቶ ይህንን ደብዳቤ የጻፉትና የላኩት አስቀድመው በመሆኑና ተዛማጅ ትርጉሙ ዘግይቶ በመውጣቱ ከጊዜ ማለፍ አኳያ አንዳንድ ነጥቦች አሁን እየተከሰተ ካለው ሁኔታ ጋር ላይጣጣሙ ይችላሉ፡፡ አንባቢያ ይህንን የጊዜ ልዩነት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ደብዳቤውን እንዲያነቡት ይሁን፡፡
_______________________________
ይህ ደብዳቤ ለሚከተሉት በግልባጭ ተልኳል፡
Hailemariam Desalegn, Prime Minister of the Federal Republic of Ethiopia
P.O.Box 1031 Addis Ababa, Ethiopia. Fax: 2511-55-20-20
Crown Prince Salman bin Abdulaziz Al-Saud, Deputy Prime Minister and Ministry of Defence
Airport Road, Riyadh 11165, Tel: 1-478-5900/1-477-7313 Fax: 1-401-1336
Jeddah Office TEL: 2-665-2400. Web site: http://www.moda.gov.sa
SAUD al-Faysal bin Abd al-Aziz Al Saud, Ministry of Foreign Affairs
Nasseriya Street, Riyadh 11124
TEL: 1-406-7777/1-441-6836 Fax: 1-403-0159
Jeddah Office Tel: 2-669-0900. Web site http://www.mofa.gov.sa
AHMAD bin Abd al-Aziz Al Saud, Ministry of Interior
PO Box 2933, Riyadh 11134
Tel: 1-401-1944 Fax: 1-403-1185
Jeddah Office
Tel: 2-687-232. Web site: http://www.moi.gov.sa
Muhammad bin Abd al-Karim bin Abd al-Aziz al-ISAMinistry of Justice
University Street, Riyadh 11137
Tel: 1-405-7777/1-405-5399
Jeddah Office TEL: 2-665-0857. Web site: http://www.moj.gov.sa
Prince Mohammed bin Nawaf Al Saud Ambassador of The Kingdom of Saudi Arabia to the United Kingdom and Ireland
Ambassador of The Kingdom of Saudi Arabia to Ethiopia
Ambassador of The Kingdom of Saudi Arabia to United States
Ambassador of The Kingdom of Saudi Arabia to Canada
 Ambassador of The Kingdom of Saudi Arabia to German
Ambassador of The Kingdom of Saudi Arabia to Norway
Ambassador of The Kingdom of Saudi Arabia to Sweden
Ambassador of The Kingdom of Saudi Arabia to Switzerland
 Ambassador of The Kingdom of Saudi Arabia to Netherlands
Ambassador of The Kingdom of Saudi Arabia to Australia 
Her Majesty Foreign and Common Wealth Office Billy Benet, League of Arab States Headquarters
His Excellency Dr. Nabil El Araby, Secretary General
Egypt Cairo – Secretariat –Tahrir Square Tel: 5752966 – 5750511, Fax: 5740331 – 5761017
PO. Box: 11642
Office of the High Commissioner for Human Rights
United Nations Office at Geneva 1211 Geneva 10, Switzerland
Fax: + 41 22 917 9022 (particularly for urgent matters) E-mail: tb-petitions@ohchr.org
United Nations High Commissioner for Refugees (UNHCR)
International Labor Organization (ILO)
International Organization for Migration (IOM) 
African Commission on Human and Peoples’ Rights (ACHPR)
Mr. Donald Yamamoto, Acting U.S. Assistant Secretary of African Affairs
Patricia M. Haslach, U.S. Ambassador to Ethiopia, Addis Ababa, Ethiopia
Mr. Christopher Smith, House of Representatives, Chairman of the Subcommittee on Africa
Human Rights Watch
Amnesty International
ከዚህ በተጨማሪ ደብዳቤው ለሚከተሉት የዜና አውታሮችና የሚዲያ ተቋማት ተልኳል
BBC, the Guardian, New York Times, 
A24MEDIA
All Africa
Bloomberg News
NCNB Africa
CNN
REUTERS AFRICA
The East Africa
African Review
VOA Ameharic
VOA-English

No comments:

Post a Comment